አቡነ ዜና ማርቆስ የአረጋውያንና የሕጻናት መርጃ ማኅበር

እኛ ማን ነን?

የአመሰራረት ታሪክ

 

የአቡነ ዜና ማርቆስ የሕጻናትና አረጋውያን መርጃ ማህበር እንዲመሰረት ምክንያት የሆነው ምን እንደሆነ በአጭሩ እገልጻለሁ፡፡ በታህሳስ ወር 2000 ዓ.ም የጉዞ መርሐ ግብር ነበረኝ፡፡ የጉዞውም መነሻ  ቦታ ልደታ ቤተ ክርስቲያን ስለነበር እዚያው ቆሜ የምጓዝበትን ሎንቺን ስጠብቅ አንዲትን ሴት ሰዎች ከበዋት አየሁ፡፡ ሴትየዋ ትንሽ ልጅ ታቅፋ ብስኩት እየሰጠቻት ነበር፡፡ የህጻንዋ ከንፈርም እየደማ በሚሰቀጥጥ ድምጽ እየጮኸች ታለቅስ ነበረ፡፡ ሰዎችም ለምን ሌላ ነገር አታበያትም እያሉ ሲያስቸግሯት ሆድ ብሷት ማልቀስ ጀመረች፡፡ "እባካችሁን ተዉኝ ለስምንት ዓመት ከስድስት ወር እናንተ መክራችሁኝ አይደለም የየዝኳት" በማለት ምርር ብላ ስታለቅስ አየኋት ፡፡ እኔም ሰዎቹ ገለል እንዲሉላት አደረኩና ለምን ታለቅሻለሽ አልኳት፡፡

 

 "ይህች ልጅ አትናገርም፡፡ አትሰማም አትቀመጥም ራሷንም መቆጣጠር አትቸልም፡፡ የምቆጣጠራትና የምመግባትም እኔው ነኝ፡፡ ሌሎች 2 ልጆች አሉኝ ፡፡ የምኖረው ኦሎንኮሚ ሲሆን ሃይማኖቴም  እስልምና ነው፡፡ ባለቤቴ ኑሮሲከብድብን የልጅቷም ነገር ተስፋ ሲያስቆርጠው እኔንም ልጆቼንም ጠሎን ጠፋ፡፡እኔም የባለቤቴም ቤተሰቦች እዚያው አካባቢ ቢኖሩም ሊረዱኝ ስላልቻሉ ወደ ልመና ገባሁ፡፡"  ብላ የማያቋርጥ ለቅሶዋን ማልቀስ ስትጀምር ስልክ ቁጥሬን ሰጥቻት የምጠብቀው የጉዞ ሎንችን ሲመጣ ወደ ጉዛዬ ሄድኩ፡፡  የልጅቷ ድምጽ እና የእናቷ የማያቋርጥ እምባ ግን ከእኔ ጋር ይጓዙ ነበር፡፡

 

ከዚያ ስመለስ ስልክ ተደወለልኝ ፡፡ "ፋጡማ ነኝ" አለችኝ፡፡ የምሰራው መርካቶ ስለነበረ ተ/ሃይማኖት ቤ/ክ ቀጠርኳት፡፡ በቀጠሮ ሰዓት ቀድማኝ ተገኘች፡፡ "እስከመቼ ድረስ ትለምኛለሽ?" አልኳት፡፡ "ይህች ልጅ እስካለች ነው፡፡ እኔ አ.አ የምመጣው ፋፋ የሚረዱኝ ሰዎች አግኝቼ ነው፡፡ ልጅቷ ከፋፋ ሌላ ምግብ መብላት አትችልም፡፡ሌሎቹ ሁለቱ ልጆቼ ጤነኛ ቢሆኑም ምግባቸውን የሚጠብቁት ከኔው ነው፡፡" ብላ ማልቀስ ስትጀምር አይዞሽ ብያት አንድ አማራጭ ሰጠኋት፡፡ራስሽን የምትችይው በልመና ሳይሆን መስራት ስትችዪ ነው ፡፡ስለዚህ ወደ ሀገርሽ ተመልሰሽ ልጅቷን አቅፈሽ መስራት የምትችይውን ስራ አስበሽ ነይ አልኳት፡፡ እኔም እስከዚያ ጓደኞቼን ሰብስቤ ነግሬ ብር አሰባስቤ እጠብቅሻለሁ አልኳት፡፡

 

ሄዳ በሚቀጥለው የቀጠሮ ቀን ስትመጣ እርሷ መስራት የምትችለውና የሚረዳት ከተገኘ ልጇን አቅፋ ጉሊት መነገድ እንደሆነ ነገረችኝ፡፡ከጓደኞቼ ያሰባሰብኩትን ብር 500 ሰጠኋት፡፡ ለጉሊት የሚሆኑ እቃዎችን ገዛዝታ እንድትሄድ ነገርኳት፡፡ በየወሩ የቤት ኪራይ ክፍያና የልጅቷንም ፋፋ በየወሩ እንደሚገዛላት ነገርኳት፡፡ እርሷም ተስፋዋ ለመለመ ጥሩ መስራትም ጀመረች፡፡ በየወሩ እየመጣችም የቤት ኪራይዋን ስትወስድ ከትርፏም ለልጆቿ ቀለብ መቻል እንደጀመረች ነገረችኝ፡፡በዚህ አይነት ስድስት ወር አለፈ፡፡

 

በቀጣይ በሰባተኛው ወር ግን የቤት ኪራይ የምትወስድበት ቀን ድረስ ሳትመጣ ስልክም ሳትደውል ቀርታ ቀኑ አለፈ፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ አንድ ቀን ስልክ ተደወለልኝ፡፡ ደዋዩ ወንድ ነበር፡፡ ፋጡማ ከዚህ ዓለም በሞት መለየቷንና  ልጆቿን አደራ ማለቷን በተለይም ደግሞ በሽተኛዋን ልጅ አደራ እንዳለችኝ ነገረኝ፡፡ የደወለልኝ ሰው ያ ጥሏት የጠፋው በሏ ነበረ፡፡

 

በሏም ሁለቱን ጤነኛ ልጆች ቤተሰቦቹ ጋር አስጠግቶ በሽተኛዋን ልጅ ይዟት  መጣ፡፡ ምን እንደማደርግ ግራ ገባኝ፡፡ ሊረዱ የሚችሉ ድርጅቶችን ፍለጋ ከወ/ሮ ውብዓለም ገብሬ ጋራ ዞርን፡፡ ሜሪጆይ የሚረዳው በተወሰነ ክልል ብቻ እንደሆነና ያውም ባሉበት እንደሆነ ገለጹልን፡፡ ብዙ ቦታ ብንሄድምም ሊሳካል አልቻለም፡፡

 

ከዚያ በመጨረሻ ሰዓት ሲ/ር ትዕግስት ከበደ  ማዘር ቴሬዛ  ስድስት ኪሎ ሂደሽ ሞክሪ አለችኝ፡፡ ከ አባትየው ጋር ልጅቷን ይዘን ሄድን፡፡ ችግራችንን ሁሉ ነገርናቸው፡፡ በብዙ መመላለስና ጭንቅ በአዘኔታ ለሚፈጠረው ችግር ተጠያቂ እንደሆንኩ ሙሉ አደራሻዬን ተቀብለው በርቺ ብለው ወደ  ውስጥ አስገብተው የሚሰሩትን የበጎ አድራጎት ስራ አሳዩኝ፡፡

 

በውስጤ አንድ ነገር ተስማኝ እነዚህ ስዎች ወንዝ ተሻግረው ወገናችው ላልሆነ ስው ይህን ሁሉ ክፍያ ሲከፍሉ እኔስ ለወገኔ ከእንሱ ይተሻለ  ማድርግ እንዳለብኝ በውሰጤ ለእግዚያብሔር ቃል ገባሁ፡፡ በዘመኔ ወገኖችቼን መርዳት እንዳለብኝ ውሰንኩ፡፡ወደ ውጪ ወጥቼ የልጆቹነ አባት ስመለክተው ራቅ ብሎ ቆሞ ጠራኝና ገባይነሽ እግዚአብሔር ይስጥሽ፡፡ ሁለቱ ልጆቼን እኔና ቤተሰቦቼ እናሳድጋቸዋለን ፡፡ ከዚህ በኋላ ካንቺ  ምንም አልፈልግም አለኝ  እና በዚያው በቆምኩበት  ጥሎኝ ሄደ፡፡

 

ውስጤ በጣም እያዘነ ወደ ቤቴ ገባሁ፡፡ ለፋጡማ  ለቤት ኪራይና ለቀለብ የተሰበሰበ 2000 ብር በእጄ ቀረ፡፡ምን ላድርገው ስል ወ/ሮ ዘውድነሽ አሰፋ አንድ ቀን እግዚአብሔር ምን እንደሚያሰራሽ አታውቂውም እና ባንክ አስቀምጪው አለችኝ፡፡ አዋሽ ባንክ አስገባሁት፡፡

ከዚያ ባጋጣሚ በብስራተ ገብርኤል ቤ/ክ ውስጥ የስነ ምግባር ትምህርት እያስተማርኩ እያለ ብስራተ ገብርኤል አካባቢ 21 የነዳያን ልጆች መጥተው ጉባኤውን ተቀላቀሉ፤ መማር ላይ  የነበሩት ሁሉም ልጆች አፍንጫቸውን ያዙ፤ በጣም ተፀየፏቸው፡፡

ከዚያ እነዚህ ልጆች ከሌላው ጋር ተቀላቅለው እንዳይማሩ ያደረጋቸው ምንድነው ብዬ ሳስብ ሊሆን የሚችለው  አለመታጠባቸው ነው፤ ትክክለኛ እንክብካቤ ማጣታቸው፤ በሰዓቱም አለመመገባቸው ንፁልብስ አለመልሳቸው ነው አልኩና ከብስራተ ገብርኤል ሰ/ት/ቤት ምግባረ ሰናይ ኮሚቴ እና  ከአጥቢያ የማኅበረ ቅዱሳን አባላት ጋር ተመካከርኩኝ፡፡ ልጆቹን በሳምንት አንድ ጊዜ ማጠብና አንድ ጊዜ መመገብ ልብሳቸውንም መቀየር እንዳለብን ተመካክረን ወሰንን፡፡በተጨማሪም  በቋሚነት ፋጡማን ሊረዷት ቃል ገብተው  የነበሩ አምስት ሰዎች ነበሩ ባንክ የገባውን ብር ለምን ቤት ውስጥ ተኝተው በችግር  ላይ ያሉትን አረጋውያንን እና ሕጻናትን አንረዳም አልኳቸው፡፡እነሱም በአሳቡ ትስማሙ፡፡ ከዚያ ቤት ውስጥ ተኘተው አይነስውር በነበሩ የ75 ዓመት አዛውንት በ አቶ ኃይሉ እና አባት በሞትባቸው ሁለት ሕጻናት ተጀመረ፡፡

 

ይህን ሀሳብ ለማስፈጸም  ወር በገባ በ3 በዜና ማርቆስ ቀን እንሰበሰብ ነበር፡፡ በዚያውም  የልጆቹን ለውጥ ስንከታተል በሳምንት አንድ ጊዜ መመገባና ማጠብ ለውጥ እንደማያመጣ አየን፡፡ ህፃናቱን አይተው ተጨማሪ ከ70 በላይ የሚሆኑ በዕድሜ ከእነሱ ተለቅ የሚሉ ሕጻናት ስለመጡ ያን ሁሉ በማጠብ ለውጥ ለማምጣት እንደማይቻል ተገንዝበን በተጨማሪም  በሳምንቱ ቅዳሜ ቅዳሜ የቀለም ትምህርት ቲቶርያል እንዲሰጣቸው ፣ በእለቱም ምሳም  እንዲመገቡ አብሳይ ተቀጥሮ  መርሀ ግበሩ ተጀመረ፡፡

 

ልጆቹን ብቻ በሳምንት መመገብና ማስተማር  ልጆቹን በዘላቂነት መለወጥ አይቻልም  ስለዚህ   መስራት የሚችሉ ወላጆቻቸውን ወደ ስራ የሚገቡበትን መንገድ ማመቻችት እንዳለብን ወሰንን፡፡  ለ03/05 ቀበሌ ስራ አስኪያጅ ለአቶ ተስፋዬ ደሴ እና ለአቶ ዘመንፈስ አማከርናቸው፡፡እነርሱም ሰብስቧቸውና እኛም እንረዳችኋለን አሉን፡፡ እኛም ሰበሰብናቸውና እዚያው ቀ/ገብርኤል ቤ/ክ ድረስ በመምጣት ተስፋ ሰጧቸው፡፡መንግስት በፈጠረላቸው አጋጣሚ እንደማንኛውም ዜጋ ተደራጅተው መስራት እንደሚችሉ ገለጹላቸው፡፡

 

ከዚያም በሳምንቱ ወላጆቹ የስነምግባር ትምህርት እያስተማርን በቂ የሆነ ስልጠና ሳያገኙ ከራጉኤል ጎልማሳ ጉባኤ እና በብስራተ ገብርኤል ሰ/ት/ቤት በተገኘ ገንዘብ ወደ ስራ ዕንዲገቡ ተደረገ፡፡  ሙያ የሚችሉና የአካባቢውን ማኅበረሰብ ባህል የሚያውቁትን ሁለት ግለሰቦች አብረን አደራጀን፡፡ጎህ ኃላፊነቱ የተወሰነ የህብረት ስራ ማህበር በሐምሌ2/2001ዓ.ም ተመሰረተ፡፡ ቀበሌ ሼድ ሰቷቸው እንጀራ መሸጥ ጀመሩ፡፡አንዷ ከ1 ወር በኋላ ጥላ ስትወጣ አንዷ ግን እስከ ዛሬ ድረስ አብራ ቆይታ በመስራት ለይ አለች፡፡ ያ አጋጣሚ ነበር እኔ ስራዬን ትቼ ከነሱ ጋር መስራት እንዳለብኝ ያስገደደኝ ፡፡

 

የሚሰባበርባቸውን እንጀራ ለልጆቻቸው ምሳ ከትምህርት ሲወጡ እንዲመገቡ ተደረገ ፡፡ ለልጆቹ መርጃ 50 ብር ለምሳ እየተቀበሉ ይመግቡ ነበር፡፡ ቲቶሪያል በየሳምንቱ ይሰጠቸው ነበር፡፡ያም ብዙ ለውጥ ሊያመጣ አልቻለም፡፡ ምሳ ሊበሉ ሲመጡ እነዚያ የለማኝ ልጆች ገብርኤል  ምሳ ሊበሉ ይሄዳሉ የሏቸው ስለነበር፡፡ ተማሪዎቹም እየተሳቀቁ መጡ ፡፡ ወላጆቻቸውም ምሳ እኛ በራሳችን መቋጠር ብንችል አሉ፡፡

 

ባጋጣሚ ከኢትዮጵየ አየር መንገድ አቶ ግርማ ዋቄና አቶ የኔነህ መጥተው ልጆቹን አይተው ተስፋ ሰጥተዋቸው ቦርሳና ቲሸርት ሰጧቸው፡፡ ማህበሩ ህጋዊ ቢሆን ብዙ ረጂ ታገኛላችሁ አሉ፡፡ ልጆቹም ይለወጣሉ አሉ;፡ ማህበሩን ህጋዊ ላማድረግ ከቤተ/ክ ወጥቶ ብዙ ሊረዱ የሚችሉ ወገኖችን ለመርዳት ይህን አላማ ይዞ ተነሳ፡፡ ህጋዊ ለማድረግ ጽ/ቤት ያስፈልገው ስለነበር በስሩ ያሉ 40 አባላትን በማሰተባበር ለ አንድ ዓመት የሚሆን  68500 ብር በማሰባሰብ በ2002 ጥቅምት 9 ቀን ተከራየን፡፡ ከዝያም   የማህበሩን እንቅስቃሴ የሚመሩ 5 የቦርድ አባላት ተመረጡ  ፐሮጀክት ፐሮፖሳልና መተዳደሪ ደንብ  አዘጋጅቶ በማቅረብ ሰኔ 16 ቀን 2002 ዓ.ም ከፌደራል የማህበራት በጎ አድራጎት ኤጀንሲ እውቅና አግኝቷል፡፡